ጌዣ ደን በገረሴ ዙሪያ ወረዳ ከሚገኙ መስህቦች አንዱ ሲሆን ከአርባምንጭ ከተማ 56 ኪ.ሜትር፤ ከገረሴ ከተማ 1 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በዛዝኤና ጎራቴ ቀበሌ ዉስጥ የሚገኝ ተፈጥሯዊና ሰዉ ሰራሽ መስህብ ነዉ፡፡ የዚህ መስህብ ባለቤት መንግስት እና የአከባቢዉ ማህበረሰብ ሲሆን የመስህቡ አጠቃላይ ሽፋን 394 ሄ/ር መሬት ነው፡፡
መስህቡ ከባህር ጠለል በላይ በ3000 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝ ሲሆን በዉስጡ በርካታ የዕጸዋት ዓይነቶች፡- እንቆቅ፣ ኮርች፣ ነጭ ባህር ዛፍ፣ ቁልቋል፣ የዝንጀሮ ወንበር፣ ጥቁር እንጨት፣ ዶቅማ፣ ግራዋ፣ ብርብራ፣ ሾላ፣ ብሣና፣ የአበሻ ጥድና የፈረንጅ ጥድ፣ ተጠቃሾች ናቸዉ፡፡ ከዚህም ሌላ ለበርካታ የዱር እንስሳት፡- ነብር፣ አነር፣ ዝንጀሮ፣ ጉረዛ፣ ሚዳቆ፣ ጦጣ፣ አጋዘን፣ድኩላ፣ ጃርት፣ ጥሪኝ፣ ጥንቸል፣ አሣማ፣ ሽለመጥማጥ፣ ጅብ፣ ምስጠ-በል/ቦዶ/ እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ እንደዚሁም እንደ ቁራ፣ ንስር፣ አሞራ፣ ጉጉት እና ሌሎችም የአዕዋፍ ዓይነቶች መኖሪያ ነዉ፡፡
በደኑ ውስጡ ለባህላዊ መዲኃኒትነት የሚያገለግሉ በርካታ ዕፅዋቶች የሚገኙ ሲሆን ከነሱም መካከል፡- አርቲሚዚያ፣ ብሣና፣ ቀበርቾ፣ ሣንጋና፣ አረንጓዴ ሻይ፣ ምድር አበባ፣ የውሻ እንሰት፣ ሀረግ ነገር፣ ሀላ፣ ኮሶ … ወዘተ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ደኑ ስያሜውን ያገኘዉ አቋርጦት ከሚያልፈው ከጌዣ ወንዝ ነው፡፡ በደኑ ማዕከላዊ ስፍራ የሲሶቴ ፏፏቴ ይገኛል፡፡ የፏፏቴው ርዝመት እስከ 40 ሜትር የሚገመት ሲሆን 10 ሜትር ስፋት አለው፡፡ ፏፏቴው በለምለሙ የጌዣ ደን ውስጥ ሆኖ ከላይ ወደ ታች ሲምዘገዘግ መመልከት የህልና ደስታን ይሰጣል፡፡
ጌዣ ደን ለተለያዩ እንስሳትና አዕዋፋት መኖሪያ ከመሆን በዘለለ የአከባቢ አየር ንብረት ለውጥ ሚዛንን ከማስጠበቅ አንፃር ከፍተኛ ሚና አለው፡፡ በተጨማሪም ለኢኮ-ቱሪዝም እንቅስቃሴ አመቺ ሆኖ ቢለማ ከፍተኛ ጥቅም ሊያስገኝ የሚችል ደን ነው፡፡ ደኑ አሁን ባለበት ሁኔታ ለጉብኝት ምቹ በመሆኑ ደርሰው ብጎበኙ አትርፈው ይዝናናሉ፡፡
ጌዣ ጥብቅ ደን

ጌዣ ደን