ጋሞ ዱንጉዛ

You are currently viewing ጋሞ ዱንጉዛ
ጋሞ ዱንጉዛ

የጋሞ ብሔረሰብ ባሳለፈው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሽግግሮች የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን እያዳበረና እየተጠቀመ መጥቷል፡፡ ከእነኝህም የጋሞ ህዝብ የፈጠራ ውጤቶች መካከል አንዱ የሆነው የሸማ ሥራ እና ሸማ ለመሥራት የሚጠቀሟቸው መሣሪያዎች ናቸው፡፡
ከረዥም ዘመናት በፊት በጋሞ አካባቢ የተጀመረው የሸማ ሥራ በኢትዮጵያ የማዕከላዊ መንግስት መመስረት አስቀድሞ የጋሞን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የአጎራባች ሕዝቦችን ጭምር ተጠቃሚ ማድረግ የቻለ እንደነበር ይነገራል፡፡ ጥንት በቁጥር ውስን የነበሩ ሸማ ሰሪዎች ከጋሞ ዞን ጨንቻ ዙሪያ ወረዳ ዶርዜ ማሕበረሰብ ልዩ ስሙ ሂርጶ ፋንጎ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ወደ ሌሎች የጋሞ አካባቢዎች እየተስፋፉ ዕውቀቱንና አሠራሩን በማስተማር አብዛኞቹ የብሔረሰቡ አባላት መተዳደሪያቸው አድርገው ወደ ሌሎች አጎራባች ብሔረሰቦች ዕውቀቱ እንዲስፋፋ አድርገዋል፡፡ በአሁን ሰዓት የሸማ ሥራ በተለይ በአዲስ አበባ ሽሮ ሜዳ አከባቢ በብሔረሰቡ ተወላጆች እና ሙያውን በቀሰሙ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በስፋት የሚከናወን ሲሆን ቦታውም እንደ አንድ የቱሪስት መዳረሻ እየተጎበኘ ይገኛል፡፡
ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት አጎራባች ብሔረሰቦችን ማለትም ጎፋ፣ ወላይታ፣ ዳዉሮ፣ አማሮ፣ ዛይሴ እንድሁም በአባያ ሀይቅ ላይ በወጎሎ (ባህላዊ ጀልባ) ወደ ጊዲቾ ጌደኦና ሲዳማ አካባቢዎች በመሻገር ቀስ በቀስ እያስፋፉ ሸማ ሥራዉን በባለቤትነት በመያዝ ሌሎች ህዝቦች ፋይዳን እንድገነዘቡና እንድጠቀሙበት አስተዋውቀዋል፡፡ በመሆኑም የሸማ ሥራ የህዝቦች የእርስ በርስ ትስስርና ግንኙነት መጠናከር የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
ጥንት በብሄረሰቡ ሰውነትን ለመሸፈን እንደ ኮባ፣ የእንጨት ልጣጭ፣ ከእንሰት ግንድ ተሸልቅቆ የሚወጣውን (zanza)፣ለራስ ከቀርከሃ ልባስ የተሠራ (gille)፣ ከእንሰትና ሌሎች ልጣጮች በተሠራ ክር መሳይ የተዘጋጀ (mashikko)… ወዘተ ይጠቀሙ እንደነበር ይነገራል፡፡ ከዚያም የበግ ቆዳ፣ (ite)፣ የፍየል ሌጦ (cala7o) ይጠቀሙት የነበረ ሲሆን አቅሙ የፈቀዳቸው በቅቤ አሽተውና አለስልሰው የጥጃ ቆዳ (galbba) ይለብሱ ነበር፡፡ በጊዜ ሂደትም ብሄረሰቡ የራሱ የሆነ ነባር ዕውቀቱን በመጠቀም ከቆዳና ሌጦ ወደ ሸማ ሥራ ተሸጋግሯል፡፡ የሸማ ሥራ የጋሞ ህዝብ ፈጠራ ውጤት ሲሆን የሸማ ሥራውን ለመሥራት የሚያገልግሉ መሣሪያዎች በብሄረሰቡ ቋንቋ “gafatee, achche, mihana, dirbbabe, wondiraashe, wondiraashe mara, ashina, mooqe, piiqe, boxe, wagumbbe, sota, qoshe, xagaga, talbabe, mooqe inxxarssi, yuusho wodoro, wottara, maxo miththi, xiree miththi, wadha miththi” ተብለው ይጠራሉ፡፡

ምላሽ ይስጡ