ቢልቦ ፍል ውሃ በጋሞ ዞን በካምባ ዙሪያ ወረዳ በጳሳ ቀበሌ ከአርባምንጭ ከተማ 134 ኪ.ሜ፤ከካምባ ከተማ 34 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ፍል ውሃው የማዜ ብሄራዊ ፓርክ አካል ነው፡፡
የቢልቦ ፍል ውሃ ፓርኩን አቋርጦ በሚያልፈዉ የማዜ ወንዝ ላይኛዉ ክፍል በፓርኩ ደቡባዊ አቅጣጫ ይገኛል፡፡ ፍል ውሃው እስከ ከ1ሜ ከፍታና 4 ሜ እስከ 5 ሜትር ዲያሜትር ስፋት ይኖረዋል ተብሎ በሚገመት ገበቴ መሳይ የተንጣለለና እጅግ ንፁህ ሆኖ በዉስጡ በርካታ ምንጮች ያሉት ነዉ፡፡ የውሃው ሙቀት መጠን እስከ 2000c እንደሚደርስ ይገመታል፡፡
ፍል ውሃው ከርቀት እንፋሎቱን እየተመለከቱ ሲቀርቡት እየተፍለቀለቀ የሚፈጥረው እንቅስቃሴ የተለየ አግራሞትን ይጭራል፡፡ በአካባቢው የሚኖሩ ማህበረሰቦች ፍልውሃውን እንደፀበል በመጠቀምና በእንፋሎቱ በመታጠን ከተለያዩ በሽታዎች ለመፈወስ ይጠቀሙታል፡፡ የቆላ ቁስል፣ እከክ፣ ጨብጥ፣ ቆዳ ላይ የሚወጡ ሽፍታዎች፣ አለርጂዎች፣ የውስጥ ደዌ የመሳሰሉ በሽታዎችን ይፈውሳል ተብሎ ይታመናል፡፡
በአካባቢው ለከብቶች ዕድገትና መኖ የሚሆን “Ado” (ጨዋማ አፈር) ለመውሰድ የሚመጡ ሰዎች ምግባቸውን በፍል ውሃው አብስለው ይመገባሉ፡፡
ቢልቦ ፍል ውሃ የሚገኝበት ማዜ ብሔራዊ ፓርክ በ1997 ዓ.ም የተመሰረተና 210 ኪ.ሜ ስኩዌር ስፋት ላይ ያረፈ ነው፡፡ የማዜ ብሄራዊ ፓርክ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘዉ የስዋይንስ ቆርኬ (Swayne’s Hartesbeest’s) ዋነኛ መኖሪያ ሲሆን በተጨማሪም አንበሳ፣ ነብር፣ ጎሽ፣ አጋዘን፣ ድኩላ፣ አሳማ የመሳሰሉ የዱር እንስሳት መገኛ ነው፡፡ ቢልቦ ፍል ውሃን ለመጎበት እስከ ስፍራው የሚያርስ ምቹ የትራንስፖርት መስመር ያለው በመሆኑ ደርሰው ይጎብኙ፡፡
ቢልቦ ፍል ውሃ

Bilbo Hot spring, Maze National Park