ማስቃላ በዓል

You are currently viewing ማስቃላ በዓል

ማስቃላ በዞኑ ብሔረሰቦች ዘንድ የሚከበር የዘመን መለወጫ በዓል ነው፡፡ በዞኑ ህዝቦች የሚከበሩ በርካታ አገር በቀል በዓላት አሉ፡፡ ማስቃላም ሆነ ሌሎች አገር በቀል በዓላቶች የራሳቸው ዓላማ፣ታሪካዊ መነሻና የአከባበር ሥርዓት ያላቸው ሲሆኑ ከበዓላቶቹ ትልቅ ሥፍራ ያለው ማስቃላ ነው፡፡ ማስቃላ በየዓመቱ እንደ ዘመን መለወጫ የሚከበርና በዚህም ህዝቡ የማክበሪያ ልማዶችንና ሥርዓቶችን በመጠበቅ የተለያዩ የጋብቻ፣እርቅ የማውረድና ሌሎች ተያያዥ ተግባራትን በመፈፀም፣እንዲዚሁም ሠላምንና አንድነትን የሚያጠናክሩ ሥርዓቶችን ተግባራዊ በማድረግ የሚከበር ነው፡፡ የማስቀላ ማክበሪያ ጊዜን ስንመለከት የዞናችን ማህበረሰቦች በየአከባቢያቸው እንደ አመቺነቱ ከሰኔ ወር ጀምረው እስከ ጥር ባለው ጊዜ ውስጥ ያከብራሉ፡፡

ማስቃላ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ህዝብ ዳብሮ ያለ፣በባህል እሴትነቱና በሥነምግባር መገንቢያነቱ ትልቅ ቦታ ያለው፣ፍትህ የሚያስገኝ፣በሰዎች መካከል መቀራረብና አንድነት የሚያጠናክር፣ላዘነም የሀዘን ማብቂያ ወቅት እና ለትዳር መመስረቻ ምክንያት ከመሆኑ አንፃር የሚሰጠው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት እሴቶች በተጨማሪ ብዙ ማህበራዊ ክንዋኔዎች መከሰቻ፣መከወኛና ማሳኪያ በዓል ተደርጎ ይወስዳል፡፡ ከዚህ አኳያ በግልም ሆነ በቡድን ለሰዎች ውስጣዊ ጥያቄዎች የሚመለሱበት ሁኔታዎች አለ ማለት ይቻላል፡፡

ቅድመ ዝግጅት
ማስቃላ የሚከበረው ከወትሮው ለየት ባለ አመጋገብ፣አለባበስና ማህበራዊ ግንኙነት በመፍጠር ነው፡፡ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ይህንን በዓል ለማክበር ዝግጅት ሲደረግ የበዓል ምግብ፣የልጆች ልብስና ሌሎች ቅድመ ዝግጅቶችን ማሟላት ይጠበቃል፡፡ አዲስ ልብስ ማሰራትና መግዛት በማስቃላ በዓል ልዩ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ ገንዘብ ማጠራቀምም ስለሚጠበቅባቸው እንደነ “matho”(እቁብ) xiire”(የወጣቶችደቦ) “Dora”(የሴቶችጥጥፈተላደቦ) ያሉ አደራጃጀቶች ተጠናክረው ለወራት ይቆያሉ፡፡

አከባበር ሁኔታ
በአሁን ጊዜ በዞኑ ሁሉም አከባቢዎች ማስቃላን ማክበር የሚጀምሩት በሁለት መልክ ነው፡፡ አንደኛው በዕለተ ሐሙስ የቅበላ ምግብ “Dishsho” አዘጋጅተው ከበሉ በኃላ በተከታታ ይባሉት ቀናት የተለያዩ ሥርዓቶችን ሲፈፅሙ ቆይተው ሰኞ ቀን እሳት ያወጣሉ፡፡
 ሁለተኛው መስከረም 16ና 17ን ጠብቀው የችቦ እሳት በማቀጣጠል ነው፡፡ ከዚህ ቀን ጀምሮ በተከታታይ ለ7 እና እስከ አንድ ወር ያለውን ጊዜ የተለያዩ ሥርዓቶች በመፈፀም ይከበራል፡፡
በጋሞ አንዳንድ አከባቢዎች የካሎ ልጆች/kalona/ ሥርዓት በባህላዊ መሪዎች/ ሀላቃ፣ሁዱጋ፣ብታንቴ/ በመምራት ማስቃላን በምረቃና የተዘጋጀውን ምግብ በመብላት መከበር መጀመሩን ያበስራሉ፡፡ ከነዚህ ልጆች የዘንድሮውን ማስቃላ እንዲመሩ የሚመረጡት እስከ ቀጣዩ ዓመት መሪ ሆነው ይቀጥላሉ፡፡ በዕለተ ማስቃላ ከብቶችም ተከልሎ በቆየው ግጦሽ ይለቀቃሉ፡፡
 ማስቀላን ሐሙስ ዕለት ማክበር የሚጀምሩ አከባቢዎች ዓርብ ቀን የሶፌ መውጫቸው ይሆናል፡፡ ቅዳሜና ዕሁድ የእርድ ሥርዓት በመፈፀምና በመጫወት ካሳለፉ በኃላ ሰኞ ጠዋት የችቦ ማቀጣጠል ተግባር ይፈፅማሉ፡፡ ከዚያም ማክሰኞ ቀን “mathe oyitho”ሥርዓት ሴቶች ወደ ቤተሰቦቻቸው ሄደው የሚጠይቁበትና ለሰው ሁሉ የ”uteththe peeshsho” /ተቀምጠውመዋል/ ቀንምይሆናል፡፡መስከረም 16 እና 17ን ጠብቀው እሳት በማውጣት የሚያከበሩ አከባቢዎች በማግስቱ እረፍት “bedinthe kamma “ ይሆንና ቀጥሎ ባለው ቀን የእርድ ሥርዓት ይከናወናል፡፡
 በዚህን ጊዜ የሶፌ /soofe/ እና እርቅ /siga/ ሥርዓቶች ይፈፀማሉ፡፡ በየአከባቢው የሚገኙት የማስቃላ ገበያዎች ሶፌ በሚወጡት ሴቶች፣ግዳዬዎችና ግርዝ በገቡ ወጣቶች ደምቀው ይውላሉ፡፡ በዚህም ሶፌ ከሚገቡት ያገባች ሴት በጓደኞቿና ዘመዶቿ ታጅባ በህዝብ ፊት አጊጣና በበቅሎ ወዲህና ወዲያ ተንቀሳቅሳ ትውውቅ ስታደርግ፣ግዳይ ጀግንነት ሥራን በፉከራና ሽለላ መግለጽ፣እንዲሁም ግርዝ የገቡ ወጣቶች የማህበራዊ ሽግግር ማድረጋቸውን የሚያረጋገጡበት ሥርዓት ይሆናቸውና ያከበራሉ፡፡
ዓመቱን ዘመድ ሞቶ ሀዘን ላይ የቆዩ ቤተሰቦች ከዋዜማ ጀምሮ ሀዘናቸውን መግለጽ ስለሚጀምሩ የሰፈሩ ሰዎች አብሮ በማልቀስና በማፅናናት ሀዘን እንዲተውና ማብቂያ /Dochche ወይም Dendo yeho/ ከተከናወነ በኃላ በዓሉን አክብረው እንዲያሳልፉ ይደረጋል፡፡ በተመሳሳይ መልክ ህዝብ ውስጥ ቅሬታ እያለ አብሮ እሳት ማውጣት፣ሥጋ ማረድ፣መጫወትና መዝናናት ስለማይቻል ቀደም ብሎ በቤተሰብ፣በሰፈርና በሌላም ደረጃ መታረቅ ያልቻሉ ለማስቃላ ሲሉ የሚተውበትና የሚታረቁበት  ይሆናል፡፡ ይህም ማስቃላ በሚከበርበት ጊዜ ከመብላትና ከመዝናናት ባሻገር ብዙ ማህበራዊ ጉዳዮች የሚፈጸምበት ሁኔታ እንዳለ ያሳያል

የሶፌ በዓል አከባበር  የበለጠ ይመልከቱ

የጮዬ ማስቃላ በዓል አከባበር የበለጠ ይመልከቱ

አሸኛኘት
የዞኑ ነባር ብሔረሰቦች ማስቃላን የሚያከበሩት ሠላምን በመፈለግ፣በዓመቱ የለፉበትን ምርት በመሰብሰብ አብሮ ማሳለፍንና መደሰትን እንዲሁም የማስቀላ ተስፋ ጽናትን በመግለጽ ባህላዊ መሪዎች በሚያደርጉት የምሥጋናና ተማፅኖ ሥርዓት ነው፡፡ በዞናችን “huduga Halaqa, maaga, bitantte, baabo/sagga/, weyecha የሚባሉት መሪዎች ማስቃላን /ዘመን መለወጫ/ መድረሱን በየአምልኮ ቦታቸውና በችቦ ማቀጣጠያ ሥፍራ ላይ በማረድ፣ምግብም ሲዘጋጅ መጀመሪያ ቀምሶና ችቦውን ቀድሞ ለኩሰው ህዝብ እንዲቀበል እንደሚያደርጉ ሁሉ በሽኝት ወቅትም ጭፍራው ባለበት በመገኘት የመሪነት ሚና ይጫወታሉ፡፡
ማስቃላ ሲሽኝም ልዩ ልዩ ሥነ -ሥርዓቶች ተፈጸመው ነው፡፡ ከእነዚህ ተግባራት ውስጥ የተወሰኑትን ለማንሳት ያህል ማስቃላን የመሩ ተሸሚዎችን በመሻርና አዲሶችን በመሾም፣ሰው ሁሉ ማስቀላን በክብር በመቀበል ላሳየው መልካም ተግባር ህዝቡን ማመስገንና መመረቅ፣ማስቃላ ለሠላምና ለብልፅግና ያላቸው በሽኝት ቀን ሰው በቤቱ በአዲስ መልክ ምግብና መጠጥ በማዘጋጀት ይበላል ይጠጣል፡፡ እንደ የአቅሙም ቤት ያፈራውን በመብላትና በመደሰት ነው የሚሸኘው፡፡ በአንዳንዶቹ የዞኑ ብሄረሰቦች መጠጥ እስከ ማስቃላ ጭፈራ ቦታ ተወስዶ በሽኝት ቀን ይጠጣል፡፡ በመጨረሻ በሰላም የመጣልን፣በሰላም ሄደ፣ በሰላም ተመለስ በማለት ይሸኙታል፡፡

ምላሽ ይስጡ