የጫሞ ሃይቅ

You are currently viewing የጫሞ ሃይቅ

በነጭሣር ብሔራዊ ፖርክ ውስጥ ከሚገኙ ተፈጥሮአዊ መስህቦችመካከል የአባያና ጫሞ ሃይቆች ተጠቃሽ ሲሆኑ ከአርባምንጭ ከተማ በደቡብና በምስራቅ አቅጣጫ በ10 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኙት ሁለት ሃይቆች በእሳተ ጎመራ አማካኝነት እንደ ተፈጠሩ ይነገራል፡፡ የአባያና ጫሞ ሃይቆች በስፋትና በጥልቀት ብቻ ሣይሆን በመልክም ቢሆን የሁለት እናት ልጆች ናቸው፡፡ አባያ በመልኩ ቀላያለና የደፈረሰ መልክ ሲኖረው ጫሞ ደግሞ የጠራ ውሃ ቀለም የያዘ ሃይቅ ነው፡፡ ጫሞ 550 ኪ.ሜ ስኩዌር ስፋትና ከ6-13ሜትር ጥልቀት ሲኖረው አባያ ደግሞ 1160 ኪ.ሜ ስኩዌር በመሸፈን ጥልቀቱ በአማካይ 13 ሜትር ነው፡፡ በሃይቁ ላይ እንደ ልጃገረድ ልጅ ጡት ጉብ ጉብ ብለው ከሚታወቁት ደሴቶች የጊድቾ ብሔረሰብ አባላት መኖሪያ የሆነው የጊድቾ ደሴት፣ጎልማካ ደሴት፣ ኦዶላ ደሴት ለአብነት ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡ ሁለቱ ሃይቆች ከአቀፉት ብዝሃ ሕይወት አዞ፣ ጉማሬና የተለያዩ ለምግብነት የሚውሉ አሳዎች ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው ለአዲስአበባና ለሌሎች የሀገራችን ክፍሎች ለምግብነት የሚቀርበው የአሣ ምርት የሚገኘው ከነዚህ ሃይቆች ሲሆን ሃይቆቹም በተፈጥሮ የተገኙ የአሣ ፋብሪካ ይባላሉ፡፡ በሃይቆቹ ላይ የጀልባ ሽርሽር ማድረግ የጎብኚውን ፍላጎት ከማርካቱ በላይ ሀሴትን ያጎናጽፋል፡፡

የእግዜር ድልድይ ከአ/ምንጭ ከተማ በ20 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ይህ ድልድይ ትልቅ የመሬት አካል ሲሆን ሁለት የተለያዩ ይዘትና ቀለም ያላቸው ሃይቆች /አባያናጫሞ/ ተገናኝተው ፀብ እንዳይፈጥሩ ለመገላገል በዳኝነት የቆመ የሚመስል አስገራሚ የመሬት አካል ነው፡፡ በዚህ የመሬት አካል ላይ ሆኖ የሁለቱን ሃይቆች ሁለንተናዊ ይዘት ለማየት የሚቻል ከመሆኑም ሌላ መንፈስን የሚያድሱና እርካታ የሚያጎናጽፉ በርካታ እንስሳትና እጽዋት በዚህ አከባቢ ይገኛሉ፡፡

ምላሽ ይስጡ