ጮዬ በዳራማሎ ወረዳ የሚገኝ ቀበሌ ሲሆን ከዳራማሎ ርዕሰ ከተማ ዋጫ በ31 ኪ.ሜ ርቀት እና ከአ/ምንጭ በ197 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ የጮዬ መስቀል በዞኑም ሆነ በሀገራችን ለየት ባለ መልኩ የሚከበር እጅግ ማራኪ የመስቀል በዓል አከባበር ሲሆን ዓይነተኛ የቱሪስት መዳረሻ ነው፡፡ የጮዬ ማስቃላ በጋሞ ብሄረሰብ ከሚከወኑ ባህላዊ ክብረ በዓላት አንዱ ሲሆን በዳራማሎና በካምባ ወረዳ የሚገኙ 8 አጎራባች መንደሮች /ቀበሌያት/ በጋራ የጮዬ ቀበሌን ማዕከል በማድረግ ይከበራል፡፡ ወቅቱ ከጥቅምት እስከ ታህሳሳ ባለው ጊዜ ስለሆነ የምርት መሰብሰቢያ፣ሰው ጠግቦ የሚበላበት፣ከብቶች እንዳሻቸው የሚቦርቁበት ነው፡፡ የመክፈቻ ( ኢቴ-ቶሆ) ስነ-ስርዓቱ ከ15 ቀናት በፊት ባለባቱ(ካዎ) ወይም ተወካይ ቁርበት(ኢቴ) በመልበስ በገበያ መሃል ቆሞ አዋጅ ያሰማል፡፡ በመቀጠል በ7ቱ አጎራባች ቀበሌያት በዙር ከተከበረ በኃላ በ14ተኛው ቀን ወዴ ማዕከሏ ቀበሌ (ጮዬ) መጥተው በቅዳሜ ዕለት የዕርድ ስነ ስርዓት ይፈጸማል፡፡ እሁድለት የመዝጊያ ስነ ስርዓት (ካንሶጋላስ) ከሁሉም መንደሮች የተመረጡት አለቃዎች(ሁዱጋዎች) በፋንጎ ላይ(የዱቡሻቦታ) በመሰባሰብ የተጣሉትን በማስታረቅ፣የተበደሉትን በመካስ ስርዓቱን፣ከጨረሱ በኃላ “ዮ…ዮ…” እያሉ በመተቃቀፍ እየዘለሉ የመጨረሻውን ምግብ (ዋላሆ) በተዘጋጀበት ተመግበዉ ሲያበቁ እንደ የማዕረጋቸው መጠን ጉቼ በአናታቸው በማሰር ካዎን አጅበው 2 ጊዜ ሜዳውን ይዞራሉ፡፡ ቀጥለው ሶፌ (በዓመቱ ትዳር የመሰረቱ ሴቶች በፈረስ ላይ በመሆን እየዞሩ የቁንጅና ውድድር ይካሄዳል፡፡ በተመሳሳይ የወንዶች የፈረስ ግልቢያ ውድድር ይካሄዳል፡፡ በመጨረሻም የጾንፌ (የችቦ) አለካኮስ በካዎ መርነት ተፈጽሞ የጮዬ ማስቃላ ይሸኛል፡፡ ይምጡ! የጋሞ ብሄረሰብ ባህላዊ እሰት ይጎበኙ፡፡ ይደሰታሉ! ይዝናናሉ!
የጮዬ ማስቃላ በዓል አከባበር

Tags: ባህል